ይኼ ሰው ጀግና ነው (Daniel Kibret )

 

ይኼ ሰው ጀግና ነው

አበሻን በአንድ እግሩ ያስቆመ፤ ለሃያ አራት ሰዓታት የመግቢያ ትኬት ፍለጋ ያሰለፈ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የብሔራዊ ቡድኑን ዐርማ የያዙ ቲሸርቶች እንዲቸበቸቡ ያደረገ፤ ሕዝብ እንደ መንጋ ንብ አንድ ዓይነት ዜማ እንዲያዜም ያስቻለ፤ ሽማግሌን እንደ ሕጻን ያስጨፈረ፤ ሕጻንን እንደ ሽማግሌ ያስተከዘ፤ የፓርቲና፣ የዘር፣ የእምነትና የባህልን አጥር አስጥሶ ወገንን በአንድነት ገመድ ያስተሣሠረ፤ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡

 

ተረስተን ነበረ፤ ረስተንም ነበረ፤ ርቀን ነበረ፤ ተርቀንም ነበረ፤ ተርተን ነበረ፤ ተረት ሆነንም ነበረ፤ እግርን ከኳስ አውጥተን ለሩጫ ብቻ አውለነው ነበረ፤ እንዲያ በሩጫ ዓለምን አስደምመን፣ ኳስ ሜዳ ግን ዘጠና ደቂቃ መሮጥ አቅቶን ደክሞን ነበረ፡፡ ሕዝባችን ከካምቦሎጆ ኳስ ወደ ዲ ኤስ ቲቪ ኳስ ፊቱን አዙሮ ነበረ፡፡ ይህንን ቀይሮ በአፍሪካ ምድር ከ31 ዓመታ በኋላ ብቅ እንድንል ያደረገ፤ በዓለም መድረክ ‹እኛም አለንበት› እንድንል ያስቻለ – ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡

 

ድሮም የዓለምን ታሪክ የሚቀይሩት ጀግና ግለሰቦች ናቸው፡፡ አገር በኮሚቴ አድጋ፣ ታሪክ በቡድን ተቀይሮ አያውቅም፡፡ የዓለም ክፉም ሆነ በጎ ታሪክ የተለወጠው የመለወጥ ዐቅም ባላቸው ግለሰቦች ማርሽ ቀያሪነት ነው፡፡ ሌላው አጃቢ፣ ተባባሪ፣ ተከታይና ፈጻሚ ነው፡፡ ቢስማርክ የሚባል ሰው ባይነሣ ኑሮ ጀርመን የምትባል ሀገር ተረት ትሆን ነበር፡፡ ካሣ (ቴዎድሮስ) የሚባል ጀግና ባይነሣ ኖሮ የዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ቅርጽ ማን ይቀይር ነበር፡፡ አብርሃም ሊንከን የሚባል ፕሬዚዳንት ባይነሣ ኖሮ የአሜሪካን የርስ በርስ ጦርነት ማን ይፈታው ነበር፡፡ ሌኒን የሚባል ሰው ባይወለድ ኖሮ ኮሚኒዝም የሚባለውን ነገር ከሃሳብ አውጥቶ ማን ሥጋ ያለብሰው ነበር፡፡ ጎርባቾቭ የሚባል ሰው ባይፈጠር ኖሮ ኮሚኒዝምን ማን ታሪክ ያደርገው ነበር፡፡ ማንዴላ የሚባል ጀግና ብቅ ባይል ኖሮ የዛሬዋን ደቡብ አፍሪካ ማን ይፈጥራት ነበር፡፡ ቴዎዶር ኸርዝል የሚባል ይሁዲ ባይነሣ ኖሮ እሥራኤል የምትባለውን ሀገር ማን እውን ያደርጋት ነበር፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የሚባሉ ንጉሥ ባይነግሡ ኖሮ ለሁለት የተከፈለችውን አፍሪካ ወደ አንድ አምጥቶ ማን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት ያደርግ ነበረ፡፡

 

በቅርቡ የታሪካችን ክፍል እየተደጋገመ አንድ ነገር ሲነገረን ነበር፤ እየተነገረንም ነው፡፡ ‹ታሪክ የሚሠራው ሰፊው ሕዝብ ነው› ይባላል፡፡ እንዴው ለመሆኑ ሕዝብ እንዴት ተሰባስቦ፣ እንዴትስ ተመካክሮ፣ እንዴትስ ወደ አንድ አቋም ደርሶ ነው ታሪክ የሚሠራው? ሕዝብ ማለትኮ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከአሶሳ እስከ ቶጎ ጫሌ ያለው ነው፡፤ የት ተዋውቆ፣ መቼ ተገናኝቶ፣ እንዴትስ አድርጎ ተደራጅቶ ታሪክ ይሠራል፡፡ ሕዝብ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃልም ተናጋሪ እንዲሆን የሚያደርጉትኮ ግለሰቦች ናቸው፡፡

 

ሕዝብ ታሪክ እንዲያራምድ የታሪክ ሞተር የሚያስነሡ አውራ ግለሰቦች ያስፈልጉታል፤ ሃሳብ የሚያመነጩ፣ ሃሳቡን የሚያሰርጹና ለሃሳቡ ግንባር ቀደም የሚሆኑ ግለሰቦች ያስፈልጉታል፡፡ የአፕል ካምፓኒ መሥራች ስቲቭ ጆብስ ብቅ ባይል ኖሮ የሞባይል ስልክን ታሪክ ማን ይቀይረው ነበር? ‹ዓለምን የቀየሩት ሦስት አፕሎች ናቸው፡፡ አዳም የበላው አፕል፣ በኒውተን ራስ ላይ የወደቀው አፕልና ስቲቭ ጆብስ የሠራው አፕል እስኪባል ድረስ የስልክን ተፈጥሮ የቀየረው እርሱ አይደለም ወይ፡፡ እነ ማርክ ዙከርበርግ ተነሥተው ፌስ ቡክ የሚባል ማኅበራዊ ሚዲያ ባይፈጥሩ ኖሮ የዘመኑን የግንኙነት ባህል ማን ይቀይረው ነበር?

 

አዎን ሕዝብ አለ፡፡ ሕዝብም ግን ታሪክ ያራምዳል እንጂ ታሪክን አይሠራም፡፡ ግለሰቦች የፈጠሩትን፣ ያሰቡትን፣ የፈለሰፉትን፣ ያመነጩትን የሚያራመደው፣ የሚያቀነቅነው፣ የሚያስፈጽመው፣ ገንዘብ የሚያደርገውና ያንን ሃሳብ፣ ፈጠራ፣ ፍልስፍና፣ ግኝትና ጥበብ የኑሮ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችለው ሕዝብ ነው፡፡

 

ቡድን ታሪክ የማይሠራበት ምክንያት ታሪክ ለመሥራት ማሰብ ወሳኝ ስለሆነ ነው፡፡ ማሰብ ደግሞ ግላዊ እንጂ በቡድን ሊታሰብ አይችልም፡፡ በቡድን መመካከር፣ መወያየት፣ ማጥናት፣ መመራመር ይቻል ይሆናል፡፡ በቡድን ማሰብ ግን አይቻልም፡፡ ሰው የተፈጠረው በየግሉ ነው፡፡ እንደ መላእክት በማኅበር አልተፈጠረምና በማኅበር ሊያስብ አይችልም፡፡ በየግል የታሰበውን ግን በማኅበር መፈጸም ይቻላል፡፡ ቡድኖች፣ ማኅበራትና ተቋማት በግለሰቦች የሚመነጩትን ሃሳቦች የሚፈጽሙ፣ የሚያዳብሩና ሕልው እንዲሆን የሚያደርጉ እንጂ ግለሰቦችን የሚተኩ ግን አይደሉም፡፡

 

አንዳንድ ማኅበረሰብ ለግለሰቦች ቦታ የለውም፡፡ ‹ሰፊው ሕዝብ› የሚባል የማይጨበጥ አካል አስቀምጧል፡፡ ሁሉንም ነገር ለሰፊው ሕዝብ ይሰጠዋል፡፡ ሕያው የሆኑትን ግለሰቦችን ገድሎ፣ ሕያው ያልሆነ ‹ሰፊ ሕዝብ› የሚባል አካልን ያነግሠዋል፡፡ ሰፊ ሕዝብ ድርሰት ይደርስ ይመስል፤ ሰፊ ሕዝብ ዜማ ያመነጭ ይመስል፤ ሰፊ ሕዝብ ይፈጥር ይመስል፤ ሰፊ ሕዝብ ይፈላሰፍ ይመስል፡፡ የሕዝብ ሆነው የቀሩ ግጥሞች፣ ታሪኮች፣ አባባሎች፣ ዜማዎችና ባህሎች እንኳን ‹ሰፊ ሕዝብ› ውጦ ያስቀራቸው ግለሰቦች ባልታወቀ ዘመንና ባልታወቀ ቦታ ያመነጩት ነው፡፡ ግን ምን ያደርጋል ስንት ባለ ዜማዎች፣ ስንት ባለ ቅኔዎች፣ ስንት ጀግኖች፣ ስንት ታሪክ ነጋሪዎች፣ ስንት ተረት ደራሲዎች ተውጠው ቀርተዋል፡፡ 

 

 

 

ይኼው የሐበሻ ጀብዱ የሚባል መጽሐፍ ቢተረጎም አይደል እንዴ ከሰላሌ የሄደ አብቹ የተባለ ጀግና ማይጨው ላይ ታሪክ መሥራቱ የታወቀው፡፡ ሰላሌ ወርዳችሁ ብታስሱ ግን አብቹን የሚያውቀው የለም፡፡ ታሪኩን ሕዝብ ወርሶታል፡፡ ‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግና ነው› በሚለው ብሂል ተውጦ አብቹ ቀርቷል፡፡  

 

ባህላችን ለቡድኖች፣ ለማኅበራትና ለተቋማት የሚያደላ በመሆኑ አያሌ ግለሰቦች እንዳይሠሩ አድርጓል፡፤ የሠሩትም ቢሆኑ እንዳይታወቁ ውጧል፡፡ ሥራቸውን እንጂ ሰዎቹን ዕውቅና አንሰጣቸውም፡፡ ለመሆኑ ይህንን ደረታችንን ነፍተን የምንኮራበትን የአኩስም ሐውልት ሐሳብ ያፈለቀው ማነው? ማን ነበር ጥበበኛው? ማን ነበር ቀማሪው? ማንስ ነበር ያቆመው? ሐውልቱን እንጂ ማንነቱን አላገኘነውም፡፡ የታደሉት ሀገሮች ሳያውቁት ለቀሩት ጀግና ወታደር ‹ላልታወቀው ወታደር› የሚል ሐውልት ይሠሩለታል፡፡ እኛስ ምን ነበረበት ‹‹ላልታወቀው የአኩስም ሐውልት ጠቢብ›› የሚል ሐውልት ብናቆምለት፡፡ ለመሆኑ ምን ምን ዕውቀት ያሉት ሰው ነው ያንን ለማሰብ የሚችለው? ታሪኩን በመላ ምት እንደገና ማነጽ ይቻላልኮ፡፡ ሰዓልያንና ቀራጽያን በምናባቸው ማሰብ ይችላሉ፤ የታሪክ ምሁራን ከግኝቶቻቸው ተነሥተው መተለም ይችላሉ፡፡

 

ልጆቻችን ሐውልቱን እንዲያደንቁ እንጂ ጠቢቡን እንዲያደንቁ አላደረግናቸውም፡፡ የጎንደርን ሕንፃ እናደንቃለን እንጂ ስለ አርክቴክቶቹ፣ ስለ መሐንዲሶቹ፣ ስለ ግንበኞቹ አውርተን አናውቅም፡፡ ግንቡ በተአምር የተሠራ ይመስል፡፡ በፋሲል ግንብ ውስጥም እነዚያ ጠቢባን እነማን እንደሆኑ ሊያሳይ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ አንዴ ፖርቹጋሎች አንዴ ግሪኮች አንዴ ፈረንሳዮች እያልን የመሰለንን ሁሉ በቡድን ስም ስንጠራ እንኖራለን፡፡ የጥበብ አሻራዎቻችን በሚገኙባቸው በታላላቅ አድባራትም ያሠሩት ሰዎች ስም እንጂ የእነዚያ ጠቢባን ስም ተረስቷል፡፡ ልክ በመጻሕፍቱ ላይ ያስጻፉት ሰዎች እንጂ የደራስያኑ ስም ተረስቶ እንደቀረው፡፡

 

 

 

ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ መመለስ የነበረብን ግን ያልመለስናቸው፡፡ እንዴው ለአፍ ታሪክ ያህል እንኳን የሐበሻ ቀሚስን ማን ጀመረው? እንጀራ መጋገርን ማን አመጣው? አምባሻ ዳቦ በማን ተፈለሰፈ? ሞሰብና ሰፌድ መስፋትን ማን አመጣው? ዋሽንትን ማን ጀመረው? ክራርንስ ማን ፈጠረው? ቆጮን ማን ጀመረው? ክትፎስ የማን ፈጠራ ነው? ገንፎንስ ማን ፈለሰፋት፣ ጭቆና ቆጭቆጫ፣ ቃተኛና ፍርፍር፣ ቆሎና ዳቦ ቆሎ ማን ይሆን ያመጣቸው? ሽሮና በርበሬ፣ ድቁስና ሚጥሚጣ፣ አዋዜና ስናፍጭ ማን ነበር አስቦ የፈለሰፋቸው? እነዚህን ጥያቄዎች ብንጠይቅ የብሔረሰቦችና የጎሳዎች ስም፣ የአካባቢና የጎጥ ስም እንጂ የግለሰቦችን ስም አናገኝም፡፡ እነርሱ ተውጠው ቀርተዋል፡፡

 

ልጆቻችን አርአያ ሊያደርጉት፣ ሊከተሉትና ሊፎካከሩት የሚችሉት ግለሰብን ነው፡፡ ማኅበርን ወይም ሕዝብን መከተል አይቻልም፡፡ ግለሰቦችን በዋጥናቸውና ባጠፋናቸው ቁጥር፣ ለጀግኖቻችን ክብርና አድናቆት በነፈግናቸው ቁጥር ሌላ ጀግና ማግኘት አንችልም፡፡ ሰነፎች ‹ሕዝብ› በሚባል የማይዳሰስ መዋቅር ውስጥ ገብተው ይደበቃሉ፡፡ ሕዝብ ተጠያቂነት የለበትምና፡፡ ሰነፎችም ተጠያቂነትን ሲፈሩ ሕዝብ ውስጥ ይደበቃሉ፡፡ እንደ ጀግኖች መሥራት ሲያቅታቸው የጀግኖችን ዋጋ ለሕዝብ ይሰጡና እነርሱም የዋጋው ተቋዳሽ ይሆናሉ፡፡

 

እኔም እሑድ ዕለት በተደረገው የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ ጨዋታ ያየሁት ይኼንን ነበር፡፡ ቡድኑን አሠልጥኖና መርቶ ለድል ያበቃው አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሳይሆን ሌሎች ነበሩ ሲመሰገኑ የነበሩት፡፡ ከሌሊት ጀምረው ወረፋ ያዙት፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ለብሰው የደገፉት፣ ጨዋታውን ያስተላለፉት፡፡ ለስፖርት ልዩ ፍቅር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበሩ ስማቸው ከፍ ከፍ ያለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከፍ እንዲሉ ያደረገው ግን ሰውነት የሚባል አንድ ጀግና ተነሥቶ ነው፡፡ በስታየሙ ውስጥ ግን ‹ሰውነት ሆይ እናመሰግናለን› የሚል ነገር አላየሁም፡፡

 

የአፍሪካ ዋንጫ ድሮም ነበረ፤ የዓለም ዋንጫ ድሮም ነበረ፤ ከሱዳን ጋር ብዙ ጊዜ ገጥመናል፤ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ደጋግመን ተጫውተናል፡፡ አሁን ማርሹን የቀየረው ማነው? ሰውነት የሚባል አንድ ታሪክ ሠሪ ነዋ፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው ጊዜ ሃያኛውን ዋንጫ ሲወስድ ስታዲዮሙ ‹ፈርጉሰን ሆይ እናመሰግናለን፤ ፈርጉሰን ጀግና ነው፤ ፈርጉሰን ለዘላለም በልባችን ይኖራል› በሚሉ መፈክሮች ተሞልቶ ነበር፡፡ ልክ ነው ፈርጉሰን የማንቸስተርን ታሪክ ለውጠውታል፡፡ ሰውነትም የኢትዮጵያ እግር ኳስን ታሪክ ለውጦታል፡፡

 

ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ

 

ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይኼን ጊዜ አበሻ

 

የተባለውኮ ያለምክንያት አይደለም፡፡ በታሪክ ውስጥ የወሳኝነት ድርሻ ላላቸው ሰዎች ክብር ለመስጠት እንጂ፡፡ ሰውነት የሚባል አሠልጣኝ ተወልዶ ይኼው ታሪክ አየን፡፡ ትረካችን ተለውጦ ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃትና አለመብቃት፤ ለዓለም ዋንጫ መብቃትና አለመብቃት ሆነ፡፡ ‹ስንት ለዜሮ ይሆን የምንሸነፈው?› የሚለው ሥጋት ቀረ፡፡ ከዚህ በላይ ምን ጀግንነት አለ? ከዚህ በላይ ምን የገጽታ ግንባታ አለ፡፡

 

ተዉ ጎበዝ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡

 

እኛ በጠባያችን አንበሳውን ካዳነው ሰው ይልቅ የገደለውን ጀግና ስለምናደርግ ነው እንጂ፡፡ እኛ በጠባያችን ችግር ሲመጣ ለግለሰቦች፣ ድል ሲመጣ ለጋራ ስለምንወስድ ነው እንጂ፤ እኛ በጠባያችን ማኅበርና ቡድን ግለሰብን ስለሚውጥ ነው እንጂ፡፡ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ በአረንጓዴ ቀለም አሻራውን ያስቀመጠ ጀግና፡፡ 

 

 

 

በቅርቡ ስለ እግር ኳስ ሜዳዎች የሥነ ምግባር ችግር በተጠራ ስብሰባ ላይ ‹አሠልጣኝ ሰውነት መሰደብ የለበትም› ተብሎ ሲነሣ አንድ የእግር ኳሱ ባለሥልጣን ‹አሠልጣኝ ቢሰደብ ምን አለበት? አሠልጣኝን መስደብ ዛሬ ነው እንዴ የተጀመረው፡፡ ድሮም እነ እገሌና እገሌ ሲሰደቡ ነበሩ›› እያሉ ሲቀልዱ ሰማሁ፡፡ ‹እንኳንም እርስዎ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አልሆኑ› ብዬ ደስ አለኝ፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት ይቅር ሲባሉ ‹ሴት መገረዝ የጀመረችው ዛሬ ነው እንዴ› ይሉ ነበር፡፡ ግግን ማስቧጠጥ ይቅር ሲባሉ ‹‹ግግ መቧጠጥ በኛ ዘመን ነው እንዴ የተጀመረው፤ ስንቱ ሲያስቧጥጥ አልነበረም እንዴ›› ይሉ ነበር፡፡ እንጥል ማስቆረጥ ይቅር ሲባሉ፡፡ እንጥል ማስቆረጥ ድሮም ነበረ፡፡ ምን አዲስ ነገር መጣ›› ይሉን ነበረ፡፡ ‹‹ ያለ እድሜ ጋብቻ ይቅር ሲባሉ ‹‹ምነው እገሊትና እገሌ ያለ እድሜያቸው አልነበረም እንዴ የተጋቡት? ዛሬ ምን አዲስ ነገር መጣ›› ይሉን ነበር፡፡ እግዜርም ዐውቆ ሰማዩን ዐርቆ ማለት ይኼ ነው፡፡

 

ለነ ወልደ መስቀል ኮስትሬ ክብር እየነሣን የኢትዮጵያ ሩጫ እንዲያድግ የምንመኝ የዋሐን ጀግናን መግደልና ታሪክ ሠሪን ማጥፋት ለምዶብናል መሰል፡፡ በላይ ዘለቀን ገደልን፤ አክሊሉ ሀብተ ወልድን ገደልን፣ አቤ ጎበኛን ገደልን፣ በዓሉ ግርማን ገደልን፣ አበበ አረጋይን ገደልን፣ ዮፍታሔ ንጉሤን ገደልን፣ አለቃ ታየን ገደልን፣ ንግሥት ዘውዲቱን ገደልን፣ ከበደ ሚካኤልን ሀብታቸውን ነጥቀን በቁማቸው ገደልን፣ ሐዲስ ዓለማየሁን መጽሐፋቸውን እያሳተምን የእርሳቸውን ንብረት ቀምተን በቁማቸው ገደልን፣ ስንቶቹ ዘፈናቸውን እየሰማን እነርሱን ግን ገደልን፤ ስንቶቹን ቲያትራቸውን እያየን እነርሱን ግን ገደልን፤ ስንቱን ስንቱን ገደልን፡፡

 

አገዳደላችን በሦስት መንገድ ነው፡፡ አሳቢውን በማጥፋት፣ ሃሳቡን በማጥፋትና ሃሳቡን በመንጠቅ፡፡ ስንት አሳቢዎች ‹ዓሣውን ለማጥፋት ባሕሩን ማድረቅ› በሚለው ብሂላችን ምክንያት ከነ ሃሳባቸው ተገደሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሃሳባቸው እንዳይሰማ፣ እንዳይነበብ፣ እንዳይሳካና እንዳይታይ በማድረግ ተገደሉ፡፡ በሌላ በኩልም አሳቢውን ዝም አሰኝቶ ሃሳቡን በመንጠቅና አሳቢው ተንገብግቦ እንዲሞት በማድረግ ስንት ጀግና አጥተናል፡፡ የነ አያ እገሌ ፈጠራዎች፣ ሃሳቦች፣ ድርሰቶች፣ ግኝቶች፣ ፍልስፍናዎች ተነጥቀው የነ አቶ እገሌ ሆነው ቀርተዋል፡፡ የነ አያ እንትና ታሪክ ለነ ክቡር እንቶኔ ተሰጥቷል፡፡ የአሳቢዎችን ጥቅም ክብርና ዝና፣ አቀንቃኞች ወስደውት ‹‹የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ›› ተብሎ ተዘፍኗል፡፡

 

አሁንም ሺ ‹ሰውነቶች› ወደፊት ተነሥተው የሀገራችንን የስፖርት መልክ እንዲቀይሩት ከፈለግን የዛሬውን ሰውነት እናወድሰው፡፡ ሰውነት ጀግና ነው፡፡ ታሪክ የለወጠ፣ ሕዝብን ያስዘመረ፣ አገርን አንድ ቋንቋ ያናገረ፤ ቡድኑን መርቶ ውጤት የዘወረ፣ ኃላፊነትን ተሸክሞ ሀገር ያስከበረ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ውጤት እንኳን ቢቀየር ሰውነት ግን የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ አንድ አይተነው ወደማናውቀው የታሪክ ምዕራፍ አድርሶታል፡፡ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ስታዲዮም በር ላይ የተሰለፍነው ሰውነት የሚባል ሰው ተስፋ ያለው ቡድን ስለሠራኮ ነው፡፡ እንዲያ ስታዲዮም ገብተን የደገፍነው ሰውነት የሚባል ሰው የሚደገፍ ቡድን ስላዘጋጀኮ ነው፡፡

 

ከነ ስሕተቱም፣ ከነ ጠባዩም፣ ከነጉድለቱም፡፡ ይኼ ሰው ጀግና ነው፡፡ 
Advertisements

About Legesse Habtegiorgis

I wish to see democratic ethiopia.
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s