ኅብረተሰቡ ወዳላስፈላጊ እንቅስቃሴ ከመግባቱ በፊት መንግሥት ለጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲሰጥ ኢፍዴሀግ ጠየቀ

መስከረም ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በአንድ ጥላ ሥር ያሰባሰበው ኢፍዴኃግ፤ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ እንዲመልስ በአፅንኦት ያስገነዘበው፤ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰኞ ዕለት በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

የግንባሩ አመራሮች  በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ፤በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥሉ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች  ማንዣበባቸውን አመልክተዋል።
‹‹ እጅግ ውስብስብና ዘርፈ ብዙ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውና መደራረባቸውም፤ አጠቃላይ  የአገሪቱን ሁኔታ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደና እየተባባሰ እንዲሄድ አድርጎታል፤›› ብለዋል።

<<ገዥው ፓርቲና መንግሥት በመገናኛ ብዙኅን አማካይነት በሚያደርጉት ቅስቀሳ አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠና በተሻለ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ቢሉም፣ በገሃድ የሚታየው እውነታና ከበስተጀርባ የሚንፀባረቁ ምልክቶች የሚያሳዩት ሀቅ ግን ከዚህ ጋር የማይጣጣም ነው፡፡>>ያለው ግንባሩ፤ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ እጅግ ተጋንኖ እየተነገረ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትም ቢሆን በአብዛኛው ሕዝብ ሕይወት ላይ ያመጣው ጠብታ ለውጥና መሻሻል አለመኖሩ፤ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል>>ብሏል።
በአገሪቱ የሸቀጦች ዋጋ እጅግ መወደድ፣ የአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም እጅግ ማሽቆልቆል፣ በጥቂት ሀብታሞችና በአብዛኛው ሕዝብ መካከል ያለው የሀብትና የኑሮ ልዩነት እጅግ እየሰፋ መሄድ፣ የአገሪቱ የሀብት ምንጭ በሙሉ በጥቂት ሀብታሞችና ኩባንያዎች እጅ መግባት፣ የአገሪቱ የግብርና የቀረጥ አከፋፈል ሥርዓት ሀብታሞችን እየደጎመ ደሃውን ሕዝብ ለስቃይና ለመከራ እየዳረገ የሚሄድ መሆኑ፤ በግንባሩ መግለጫ   ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

<<መንግሥት በቀየሰው የመሬት፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የፋይናንስና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፖሊሲዎቹ ድክመትና የአሠራር ችግሮች፣ የሚመጣበትን ኪሳራና ሸክም፤ በደሃው ሕዘብ መስዋዕትነት የማካካስ ሁኔታ እየተከተለ ነው >>ሲልም ኢፍዴሀግ ገዥውን መንግስት ወቅሷል ፡፡

ቀደም ሲል የፀደቀውና ሲያወዛግብ የቆየው የከተማ ቦታ ይዞታና አጠቃቀምን አስመልክቶ የወጣው አዋጅም፤ የነዋሪውን ሕዝብ የዜግነት መብትና ክብር የገፈፈ፣ ሕዝቡን አየር ላይ ያስቀረ  እና የገጠሩንም ሕዝብ በጎጆውና በርስቱ ውሎ ለማደር ዋስትና ያሳጣበት ደረጃ ላይ ያደረሰ መሆኑን፤ ግንባሩ አብራርቷል፡፡

<<መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ሰፊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል በሚሉት በአነስተኛና ጥቃቅን የሥራ ፈጠራ ዘርፍም ቢሆን ፤ተደራጅቶ ለመሥራትና የመሥርያ ገንዘብ ለማግኘት የገዥው ፓርቲ አባልና ደጋፊ የመሆን ቅድሚያ ግዴታ ነው ይላሉ>> የሚለው የግንባሩ መግለጫ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከመደራጀት ጋር በተያያዘ ዜጎች የፖለቲካ መስፈርት እየቀረበላቸው ነው ፤የኢሕአዴግ ወይም የፎረሞች አባል ለመሆን መጠየቅ፤ የአደባባይ ምስጢር ነው፤›› ብሏል።

በአገሪቱ የግንባታውን ዘርፍ ጥቂት ኩባንያዎችና የፓርቲው ደጋፊዎች በበላይነት የተቆጣጠሩት በመሆኑም፣ የተቀረው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ የእነዚህ ክፍሎች አገልጋይና የጉልበት ሠራተኛ መሆን ብቻ  እንደሆነ፤ የግንባሩ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ከተሞች -የመኖርያ ቤት እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱንና  በየከተማው በልማትና በኢንቨስትመንት ስም የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር መበርከቱን የጠቆሙት አመራሮቹ፣< የተሻለ የመኖርያ ቤት ይሰጥሃል> የተባለው ደሃው ሕዝብ ቤት አልባ ሆኖ የትም ሲወድቅ ፤በደሃው ሕዝብ ስም የሚሠራው የኮንዶሚኒም ቤት ለባለሀብቶች፣ ለባለሥልጣናት፣ ለገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ለወገን ዘመዶቻቸው እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሙስና የሥርዓቱ ከፍተኛ መገለጫ እየሆነ መምጣቱን፣ የመልካም አስተዳደር እጦትም  ዜጎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ብሶትና ምሬት ውስጥ እየከተተ መሆኑንም  ኢፍዲሀግ አመልክቷል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በሚኖሩ ዜጎች፣ በአርሶ አደሮች፣ በአርብቶ አደሮች፣ በንግዱ ማኅበረሰብና በመንግሥት ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው መፈናቀል፣ መሰደድ፣ የሀብትና ንብረት መዘረፍ፣ ያለአግባብ መታሰር፣ መቀጣት፣ መንገላታት፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስና መረገጥ፤እጅግ እየተባባሰ መምጣቱንም ግንባሩ በመግለጫው አስረድቷል፡፡

የሕግ በላይነት መጥፋት፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በፖለቲካ ወገንተኝነትና ታማኝነት ላይ የቆመ መሆን፣ የሚዲያና የፕሬስ ነፃነት መታፈን፣ የጋዜጠኞች፣ የፓርቲ አባላትና አመራሮች በረባ ባልረባው ነገር እየተለቀሙ መታሰርና መሰደድ እየጨመረ መሄዱንም ፤የግንባሩ አመራሮች ገልጸዋል።

 

ከዚህም ባሻገር አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ  ከጎረቤት አገሮች ጋር  ተደቅነውባታል ያሉትን  ችግሮችም በስፋት አብራርተዋል።

በመሆኑም የአገሪቱን ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና የሸቀጦችን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር የሚያስችል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈለግ  የኢፍዴሀግ መሪዎች አሳስበዋል፡፡

<<በአገሪቱ እየታየ ያለው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ መሽመድመድ፣ የመገናኛ ብዙኅን ነፃነት  መጥፋት፣ የግል ፕሬስ መታፈን፣ የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስና መረገጥ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በፖለቲካ ታማኝነትና ወገንተኝነት መቆም ከፍተኛ አደጋ እየሆነ የመጣ ስለሆነ፤ አስቸኳይ መፍትሔና የለውጥ ዕርምጃ እንዲወሰድ ኢፍዴኃግ ይጠይቃል፡፡>> ይላል- የግንባሩ መግለጫ።

በየአካባቢው በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር ወይም በጎሳ ልዩነት፣ እንዲሁም በአካባቢ ባለሥልጣናትና በካድሬዎች ግፊትና ቅስቀሳ እየተከሰቱ ላሉት ግጭቶች ተገቢው መፍትሔ እንዲፈለግም  ፤ ግንባሩ ጠይቋል።

የአገር ሀብትና ንብረት በኢንቨስትመንት ስምና በሙስና እንዲባክን ማድረግ፣ በፖለቲካ ድርጅት አቋም፣ በቡድንተኝነትና በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ መዋቅር በመፍጠር የአገር ሀብትና ንብረት እየዘረፉ ለጥቂቶች ማስተላለፍ  እንዲቀምም፤ የግንባሩ መሪዎች  አስጠንቅቀዋል።

‹‹በብሔር ላይ የተመሠረቱ የግል ባንኮች መበራከት፤ ነገ በአገር አንድነት ላይ የሚያስከትለውን ጦስ መንግሥት ያውቃል ወይ?›› በማለት በአጽንኦት የጠየቁት የኢፍሀዲግ መሪዎች፤በዘረኝነት የተመሠረተ የኢኮኖሚ መዋቅር ሊፈርስና ሊበጠስ እንደሚገባ መክረዋል።

በደሃው ሕዝብ ላይ በየጊዜው እየጨመረ ያለው ተደራራቢ የግብርና የታክስ አከፋፈል ሥርዓት እንዲሻሻል፣  በረሃብና በምግብ እጥረት ችግር <የወገንና የመንግሥት ያለህ!> እያሉ ላሉ ችግረኞች በአስቸኳይ አስፈላጊው ዕርዳታና ድጋፍ እንዲሰጥ፣ በመኖርያ ቤት እጥረት እየተሰቃዩ ያሉ ቤት አልባ ዜጎች በአስቸኳይ ቤት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠርም፤ ጥያቄ አቅርበዋል።

መግለጫው በመጨረሻም፦<< በአገርና በሕዝብ ደኅንነት ላይ የተደቀነውንና እያንዣበበ ያለውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችንና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመመከት የሚያስችል ትኩረትና ሁለንተናዊ ዝግጁነት ሊኖር ይገባል፤›› ይላል።

የፓርቲው መሪዎች ሀሳባቸውን ሲቋጩም ‹‹አደጉ የተባሉ ሰዎችን በጥይት ፍጥነትም የማንደርስባቸው ርቀት  ድረስ ሄደዋል፡፡ ደሃው ግን ሦስትና አራት ሜትር ወደታች እየወረደ ነው፡፡ መንግሥትም ከነጋዴው ጋር ደባል ሆኖ እየሠራ ነው፤››  ብለዋል።

‹‹የራበው ውሻ ጌታውን ይነክሳል›› ያሉት የፓርቲው ሊቀ-መንበር አቶ ግርማይ፤ ኅብረተሰቡ ወዳላስፈላጊ  እንቅስቃሴ ከመግባቱ በፊት መንግሥት ለጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

 

Advertisements

About Legesse Habtegiorgis

I wish to see democratic ethiopia.
This entry was posted in Ethiopia news. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s