የኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚና ሰባት ኃላፊዎች ከአገር እንዳይወጡ ታገዱ

–    ቃላቸውን ሰጥተው በ10 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀዋል
–    በተርሚናል ውስጥ ያሉ ሱቆች ጨረታ ጊዜ ማለፉ እያነጋገረ ነው

በታምሩ ጽጌ

ከዓመታት በፊት ወጥቶ ከነበረ ጨረታ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ዓለሙና ሌሎች ሰባት የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከአገር እንዳይወጡ መታገዳቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡ ኃላፊዎቹ ከአገር እንዳይወጡ የታገዱት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለደኅንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ባለሥልጣን የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምርያ መስከረም 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ደብዳቤ በመጻፉ ነው፡፡ መምርያው ደግሞ ለቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ መስከረም 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት መታገዳቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል

እግድ እንደተጣለባቸው ምንም መረጃ ያልነበራቸው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ዓለሙና የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይላይ ገብረፃዲቅ፣ ከመስከረም 22 ቀን ጀምሮ ለአራት ቀናት በዱባይ ይካሄድ በነበረው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት መስከረም 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ለመሄድ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ ከአገር መውጣት እንደማይችሉ ተነግሯቸው መመለሳቸውንና አብረዋቸው የነበሩት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተርና አንድ ኤክስፐርት ግን መሄዳቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚውን ጨምሮ ስምንቱ የማኔጅመንት ከፍተኛ አመራሮች ከአገር እንዳይወጡ እግዱ የተጣለባቸው፣ ድርጅቱ ከዓመታት በፊት ለመንገደኞች ሸኚዎችና ተቀባዮች ትኬት ሽያጭ ከወጣ ጨረታ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ በወቅቱ ጨረታውን አሸንፎ የነበረው ሴፍቲ ራይት ፓርኪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ካቀረበባቸው ክስ ጋር በተገናኘ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

ምንጮች እንደሚሉት፣ በወቅቱ ለወጣው ጨረታ ስድስት ተጫራቾች ተወዳድረዋል፡፡ አምስቱ ተወዳዳሪዎች ለጨረታው ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር (በዓመት ገቢ የሚያደርጉት) ሲያቀርቡ፣ ሴፍቲ ራይት ፓርኪንግ ግን ስድስት ሚሊዮን ብር ያቀርባል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ለሥራው ጨረታ ሳያወጣ ራሱ በሚሠራበት ጊዜ በዓመት የሚያገኘው ገቢ ከሁለት ሚሊዮን ብር በልጦ ስለማያውቅ፣ ሴፍቲ ራይት ፓርኪንግ ያቀረበው ስድስት ሚሊዮን ብር “የተጋነነ ነው፤ ድርጅቱ ሥራውን ስለማያውቀው ነው እንጂ ይህንን ያህል ሊያቀርብ አይችልም፤” በሚሉና “ባቀረበው ዋጋ ይሰጠው” በሚሉ ወገኖች ማኔጅመንቱ ለሁለት ተከፍሎ እንደነበር ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

የተወሰነው የማኔጅመንት ቡድን ድርጅቱ ባቀረበው የገንዘብ መጠን እየሠራ እንዲታይ በመወሰኑ፣ አሸናፊው ድርጅት ሥራውን እንዲቀጥል መደረጉን የገለጹት ምንጮች፣ ድርጅቱ ግን ሥራውን በወቅቱ መጀመር ባለመቻሉ ያስያዘው የጨረታ ማስከበሪያ (ቢድቦንድ) እንደሚወረስ ሲነገረው ሥራውን መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ሥራውን በጀመረበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዓረብ አገሮች ማለትም ወደ ኳታርና ሌሎችም አገሮች የነበረውን በረራ መሰረዙን ተከትሎ፣ ሴፍቲ ራይት ፓርኪንግ “ዋና የገቢ ምንጭ የሆኑት አየር መንገዶች በመሰረዛቸው ገቢዬ ቀንሷልና በተወዳደርኩበት የገንዘብ መጠን መክፈል አልችልም፤” በማለት ማመልከቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የኤርፖርቶች ድርጅት ማመልከቻውን ተመልክቶ በገበያ ልማት መምርያ በኩል ጥናት ሲያደርግ፣ ድርጅቱ ያስገባው ማመልከቻ ትክክል መሆኑንና መክፈል እንደማይችል በማረጋገጡ፣ ለሦስት ወራት ቅናሽ እንዲደረግለት ወስኖ ድርጅቱ በወር ምን ያህል ማስገባት እንዳለበት ለማወቅ ሌላ ጥናት ማድረግ ይጀምራል፡፡

በተደረገው ጥናት ሴፍቲ ራይት ፓርኪንግ በዓመት አራት ሚሊዮን ብር እንደሚያገኝ በመረጋገጡ፣ በተደረገለት የሦስት ወር ቅናሽ ላይ ሁለት ወራት ተጨምሮለት ከሁለት ወር በኋላ እንደሚለቅ ሲነገረው፣ ድርጅቱ ግን በቅናሹ መቀጠል እንዳለበት በመከራከር ላይ እንዳለ አዲስ ጨረታ ወጥቶ ለሌላ አሸናፊ ድርጅት በመሰጠቱ፣ ሴፍቲ ራይት የኤርፖርቶች ድርጅት ኃላፊዎችን መክሰሱንና ክሱም ገና በሒደት ላይ መሆኑን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ሴፍቲ ራይት ፓርኪንግ በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ላይ ያቀረበውን ክስ ተከትሎ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የድርጅቱን ስምንት ኃላፊዎች ሐምሌ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. በማስጠራት፣ ድርጅቱ ቀደም ሲል ያወጣውንና ሴፍቲ ራይት ፓርኪንግ ያሸነፈበትን ጨረታ በሚመለከት ጥያቄ እንዳቀረበላቸው ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

ተጫራቹ ያቀረበው ተገቢ ያልሆነ የመጫረቻ ዋጋ ከተረጋገጠ በኋላ ጨረታውን ወዲያው ማቋረጥ ሲገባቸው ለምን እንዳራዘሙለት፣ ያለሥልጣናቸው ቅናሽ በመፍቀድና በድርጅቱ ላይ ኪሳራ እንዲደርስ ማድረጋቸውን በመግለጽ ቃላቸውን እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ፣ እያንዳንዳቸው የአሥር ሺሕ ብር ዋስ ጠርተው እንዲለቀቁ መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚውና የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ዳይሬክተሩ ከቫት ጋር የተገናኘ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን የድርጅቱ ማኔጅመንት የሚወጡ የጨረታ ዓይነቶችን ተመልክቶ የመጨመርና የመቀነስ ሥልጣን እንዳለው የድርጅቱ መመርያ እንደሚያመለክት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ውስጥ ያሉት የንግድ ሱቆች  የጨረታ ጊዜያቸው አንድ ዓመት እንዳለፈው ለቦርዱ በማሳወቅ፣ በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም. ጨረታ ማውጣቱን ተከትሎ፣ በቀድሞው ጨረታ አሸንፈው በመሥራት ላይ ያሉት ለንደን ካፌና ካንትሪ ትሬዲንግን ጨምሮ 23 ድርጅቶች ድርጅቱን ከሰው ነበር፡፡ የድርጅቱ ማኔጅመንት የተወሰኑ አባላት ነባሮቹ ነጋዴዎች እንዲቀጥሉ ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ አዲስ ጨረታ መውጣት እንዳለበት ሲሟገቱ ባለበት ሁኔታ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ጨረታው ለሦስት ወራት እንዲቆም ባዘዙት መሠረት ውዝግቡ መቆሙ ታውቋል፡፡ ከቦርድ ሰብሳቢዋ ትዕዛዝ በኋላ ክስ መሥርተው የነበሩት 23 ነባር ድርጅቶች ክሳቸውን አቋርጠዋል፡፡

በተርሚናሉ ውስጥ ለሚገኙት 37 የንግድ ሱቆች ወጥቶ ለነበረው ጨረታ 600 ተጫራቾች ቀርበው እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፣ በንግድ ሱቆች ውስጥ የዶላር፣ የሐሺሽ፣ የናርኮቲክስ፣ የሜርኩሪና ሌሎች ሕገወጥ ንግዶች ሳይካሄዱ እንደማይቀር ጥርጣሬ እንዳለ ምንጮች ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ለሦስት ወራት ብቻ እንዲቆም ያደረጉት የጨረታ ውዝግብ ጉዳይ ሦስት ወሩ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ አሁንም ዝምታ መመረጡ ግልጽ እንዳልሆነና በተለይ ሕጋዊ ሆነው ጨረታውን የተወዳደሩ ነጋዴዎች “ማንን ነው የምንጠይቀው?” በማለት ግራ መጋባታቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ኃላፊዎች ከአገር እንዳይወጡ የታገዱት ቀድሞ በነበረው ጨረታ ላይ ስህተት ተፈጽሟል በሚለው ብቻ ሳይሆን፣ ለሦስት ወራት የታገደው በግንቦት 2004 ዓ.ም. የወጣው ጨረታ ጊዜውን ጠብቆ ባለመውጣቱ ምክንያት ሊሆንም እንደሚችል የምንጮች ግምት ነው፡፡

Source.Reporter

Advertisements

About Legesse Habtegiorgis

I wish to see democratic ethiopia.
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s