ፈረንጅ ነውኮ

ማክሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓም የተዘጋውን የኢንተርኔት መሥመር ለማስከፈት እዚህ አያት መንገድ ጉርድ ሾላ ያለው የቴሌኮሙኒኬሽን ቅርንጫፍ ሄድኩላችሁ፡፡ በጠዋቱ ሠልፉ ለጉድ ነው፡፡ ምናለ የቀበሌ መስተዳድሮች ለአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሥልጠና ቢሰጡ? ቀበሌ እንኳን የጠፋው ሰልፍ እዚህ ከነ ሙሉ ክብሩ ይንጎማለላል፡፡ አዛውንትና አሮጊቶች እግራቸው እየተንቀጠቀጠ ውጭ በብርድ ቆመዋል፡፡ ያውም ከሠላሳ ደቂቃ በላይ፡፡

እንደምንም ተራ ደርሶኝ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ እዚያም ለካስ ሌላ ሰልፍ አለ፡፡ ደግነቱ እዚህ የምትሰ ለፉት ተቀምጣችሁ ነው፡፡ ፊት ለፊታችን የተገተሩት ኮምፒውተሮች ብዙዎች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ሰዎች ግን ሦስት ኮምፒውተር ለአንድ ሠተራኛ እንዲደርሳቸው ሆነው ነው፡፡ አሁን እነዚህ ሁሉ ኮምፒውተሮች የሚሠራባቸው ከሌለ ለምን ተገዙ? ከተገዙስ ለምን አይሠሩም? ማን መልስ ይሰጣችኋል? ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ አለ ያገሬ ሰው፡፡

 

እኛ ካሁን ካሁን ደረሰን እያልን ማርያም ማርያም ስንል አንድ ሕንድ ቦርሳውን አንጠልጥሎ መጣ፡፡ የሚያስተናግዱን ሴትዮ ቀጥ አድርገው ወደ መስተንግዶው ወንበር ወሰዱት፡፡ ይታያችሁ ውጭ አያሌ አዛውንትና አሮጊቶች ቆመዋል፡፡ ውስጥ እኛ ተቀምጠናል፡፡ አላስቻለኝምና ሰውዬውን ተራ እንዲይዝ በሚያውቀው ቋንቋ ነገርኩት፡፡ ወዲያው አስተ ናጋጇ «ተወው» አሉኝ፡፡ ገርሞኝ ወደ እርሳቸው ሄድኩና «ለምን?» ስል ጠየቅኳቸው፡፡ «ፈረንጅኮ ነው» ብለውኝ እርፍ፡፡

ይሄኔ አዝኜም ተናድጄም «እና ፈረንጅ ቢሆንስ፤ ፈረንጅ አይሰለፍም? ተራ አይጠብቅም? መመሪያችሁ ያዝዛል?» ደረደርኩት ጥያቄዬን፡፡ ምንም አልመሰላቸውም፡፡ «አንድ ሰው ነው ቢገባ ምናለ» አሉኝ «እዚህኮ በቡድን የመጣ የለም፡፡ ሁላችንም አንዳንድ ሰዎች ነን፡፡ እንደዚህ ለሰው ካሰባችሁ ለምን እዚያ ወገባቸው የሚንቀጠቀጠውን አሮጊቶችና አዛውንት አታስቀድሟቸውም» አልኳቸው፡፡ «እነርሱማ የኛው ናቸው እርሱ ግን ፈረንጅ ነው»

ይኛን ጭቅጭቅ ሰምተው የቦታው ኃላፊ ይመስሉኛል ሌላ ሴትዮ መጡ፡፡ «ምን ሆናችሁ ነው?» አሉን፡፡ ነገርኳቸው፡፡ «አይዞህ ይደርስሃል፤ አትጨቃጨቅ፡፡ ምናለ አንድ ሰው ነው፡፡» ማለሳለሳቸው ነው፡፡ ሌላም ሰውዬ «አንድ ሰው ነው ማለት ምን ማለት ነው? እኛስ ስንት ሰው ነን?» ሲል ሁላ ችንም ሳቅን፡፡ ሌላ ተስተናጋጅም «ቅድም እኒያ አሮጊት በምርኩዝ መጥተው አላስገባም አላላችሁም? እኛ አይደለን ይግቡ ግዴለም ብለን ያስገባናቸው? እርሳቸው ለሀገራቸው ሠርተዋል፤ ልጆች አሳድገዋል፤ በእድሜም አርጅተዋል፤ ለእርሳቸው ሳታዝኑ እንዴት ለሕንዱ አዘናችሁለት?» ሴትዮዋ ነገሩ መክረሩን ሲያውቁ፡፡

«በቃ ተውት፤ ምናልባት ተራ ያዝ ለማለት ቋንቋውስ ከየት ይመጣል ብላችሁ ነው» ብለው ሁላችንንም አሳቁን፡፡

እኛም «ምናልባት ቴሌ ኮሙኒኬሽን ኢትዮ ቴሌኮም ተብሎ ፈረንጆቹ (ፈረንሳውያን) አስተዳደሩን ስለ ያዙት ለፈረንጅ ቅድሚያ እንዲሰጥ ታዝዞ ይሆናል እያልን ወረፋችንን ይዘን ትንታኔያችንን ቀጠልን፡፡

አንዳንድ ወረፋ ያዦች ብዙ ቦታ ሲሄዱ ፈረንጅ ሲፈተሽ እንደማያዩ ተናገሩ፡፡ ሌሎችም በቤተ ክርስ ቲያን ከፈረንጅ ጋር ለሚጋቡት የተለየ ክብር እንደሚሰጥ፣ ለሌላው የማይደረግ የቀኖና ማስተካከያ እንደ ሚደረግ ያጋጠማቸውን አወጉን፡፡ ሌሎችም በየፋብሪካውና በየግንባታ ኩባንያው በስመ ፈረንጅ የመጡ ነጮች ሠራተኛውን ሲደበድቡና ሲበዘብዙ ፈረንጅ በመሆናቸው ብቻ ሃይ የሚላቸው እንደሌለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአካባቢው ለሚገኙ የመስተዳድር አካላት ሲያመለክቱም ከአበሾቹ ይልቅ ፈረንጆቹን መስማት እንደ ሚመርጡ ይተርኩ ጀመር፡፡

ይሄኔ ነው የኦፕራ ገጠመኝ ትዝ ያለኝ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ታዋቂዋ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር አዘጋጅ ኦፕራ ዊንፍሬ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ያጠማትን ነገር ኀዘን በተሞላበት ሁኔታ የገለጠችበትን ዝግጅት አቅርባ ነበር፡፡ እርሷ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ አራት ጠባቂዎችን ቀጥራ ነበር፡፡ ችግሩ ቀጣሪዋ ኦፕራ ጥቁር፣ ተቀጣሪዎቹ ደግሞ ነጮች ሆኑ፡፡ ኢትዮጵያ ደርሳ ከአውሮፕላን ማረፊያው ጀምሮ ኦፕራ ያላገኘችውን ክብርና መስተንግዶ እርሷ የቀጠረቻቸው ነጭ ጠባቂዎቿ እንዴት ያገኙት እንደነበር በኀዘን ገልጣ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት አምባ ትባላለች እንጂ ራስዋን እንደ ጥቁር አፍሪካ አካል አድርጋ አትመለከትም የሚል ትችትም ሠንዝራ ነበር፡፡

አንዲት አፍሪካውያን በሚበዙበት ድርጅት የምትሠራ ወዳጄ አብራት ለምትሠራው አፍሪካዊት እኅቷ የቤት ሠራተኛ ታፈላልግላታለች፡፡ የቤት ሠራተኛዋ የቀጣሪዋን የሥራ ቦታ ስታውቅ ደሞዙን ሞቅ አደረገችው፡፡ ያችም የሰው ሀገር ሰው አማራጭ ስላልነበራት ተስማማች፡፡ ሥራ የምትጀምርበትን ቀን ቆረጠና የኔ ወዳጅ የቤት ሠራተኛዋን ይዛ ወደ ቀጣሪዋ ቤት ሄደች፡፡

እዚያ ስትደርስ የቤት ሠራተኛዋ ሃሳቧን ቀየረች፡፡ «ቤቱ ሩቅ ነው፤ ትልቅ ነው» የሚሉ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ዓይነት ምክንያት መደርደር ጀመረች፡፡ ብትባል ብትሠራ አልነካውም አለች፡፡ በነገሩ አዝ ነው ቀጣሪዋና አስቀጣሪዋ ተሰነባበቱና አስቀጣሪዋ ያችን የቤት ሠራተኛ በመኪናዋ ይዛት ወጣች፡፡

መንገድ ላይ «ከተስማማሽ በኋላ ሃሳብሽን እንዴት ትቀይሪያለሽ? ለምን መጀመርያ አልነገርሽኝም ነበር» አለቻት አስቀጣሪዋ፡፡ የቤት ሠራተኛዋም «እኔ ፈረንጅ መስላኝ ነበር እንጂ» ስትል አስቀጣሪዋ በንዴት መኪናዋን አቆመችና «አንቺ ከደመወዝሽና ከሥራው እንጂ ከሴትዮዋ ቅጣትና ጥቁረት ምን አለሽ?» አለቻት፡፡ «እንዴ እኔ ጥቁር ቤት እሠራለሁ ማለት አፍራለሁ» ብላት ዕርፍ፡፡ እንግዲህ እርሷ ነጭ መሆንዋ ነው፡፡

አንዱ ችግራችን ራሳችንን የጥቁር አፍሪካ አካል አድረገን አለማየታችን ይመስለኛል፡፡ ስለሌሎች አፍሪካ ውያን ስናወራ እንኳን «ጥቁሮች» እያልን ነው፡፡ የመንግሥቱ ለማ ባሻ አሸብር እንደሆኑት ማለት ነው፡፡ ጥቁርነታችንን አለመቀበላችን ለነጭ የተለየ ቦታ እንድንሰጥ አድርጎናል፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮ ጵያውያን ወደ ውጭ ሀገር እየሄድን ለመኖር የተለየ ጉጉት ካደረብን ካለፉት ዐርባና ሠላሳ ዓመታት ወዲህ ከፈረንጅ ጋር መሥራት፣ ፈረንጅ ሀገር መሄድ፣ በፈረንጅ ቋንቋ መናገር፣ የፈረንጅ ልብስ መልበስ፣ የፈረንጅ ምግብ መብላት፣ ፈረንጅ ማግባት፣ ፈረንጅ መቅጠር፣ የፈረንጅ ፊልም ማየት፣ የፈረንጅ ስም ማውጣት፣ ፈረንጅ ማስተናገድ፣ የክብርና የደረጃ ማሳያዎች እየሆኑ መጥተዋል፡፡

ዛሬ ዛሬ ያ በሽታ አድጎ አድጎ ተቋሞቻችንና ዩኒቨርሲቲዎቻችን ፈረንጅ መቅጠር፣ በፈረንጅ መመራትና አስተዳደሩን ለፈረንጅ መስጠት የሥልጣኔና የደረጃ መሳያ አድርገውታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ይቺ በመዳህ ላይ ያለቺው የፊልም ጥበባችን እንኳን በፈረንጅ ቻይናዎች እየተሞላች መጥታለች፡፡ በሙዚቃ ክሊፖቻችንም ፈረንጅ እስክስታ ሲመታና ሞሰብ ከብቦ እንጀራ ሲመገብ ማሳየት የተወዳጅነቱ ማሳያ ሆኗል፡፡

ስለ አድዋና ማይጨው፣ ስለ ሦስት ሺ ዘመን ነጻነትና ስለ ቅኝ አለመገዛት የምናወራው ሁሉ እንደ ላሜ ቦራ ተረት እየሆነ መጥቷል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶች እንኳን ሲፎካከሩ «እዚህ ቤት ነጮች ብቻ ናቸው የሚያዘወትሩት» መባልን የክብራቸው መለኪያ ሲያደርጉት ታያላችሁ፤ ትሰማላችሁም፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤተ እምነቶቻችን እንኳን ለሀገሬው ሰዎች አይነኩም አይዳሰሱም የሚባሉትን ነገሮች ለፈረንጆች መፍቀድና ማሳየት ነውር አይመስላቸውም፡፡

ይሄው ለነጮች አልገዛም ብሎ የኖረው መሬት እንኳን ዛሬ ነጭ በነጭ እየሆነ አይደለ፡፡ መሬት ወሰዱ ሲባል የምሰማቸው ሁሉ «ፈረንጆቹ» ናቸው፡፡ መሬት ወሳጆቹም ነጮች፣የሚዘራውም ነጭ፣ የሚሸ ጠውም ለነጭ፡፡

እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ በተለይ በምዕራብ ሀገሮች ቆይተው የሚመጡ ዳያስጶራ ኢትዮ ጵያውያን ከፈረንጅ ጋር መኖር ያረንጅ ይመስል ራሳቸውን እንደ ፈረንጅ መቁጠራቸው ነው፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤት ስትሄዱ፣ ወይም አንዳንድ ጉዳይ የሚፈጸምባቸው ቢሮዎች ስትገቡ ዳያስጶራ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንዴማ እነርሱ ከውጭ ስለሚመጡ ብቻ የሊዝ ዋጋ ለእነርሱ እንዲቀንስ፣ መሬት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፤ መኪናና የቤት ዕቃ ያለ ቀረጥ እንዲ ያስገቡ፣ በየቢሮው የተለየ አስተያየት እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ባለፈው እንኳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፋሲካ ሰሞን ሰብስቧቸው ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳችም ነገር ሳያነሡ ለዲያስጶራ ይሄ ይደረግለት፣ ይሄ ይፈቀድለት፣ ይሄ ይሟላለት እያሉ ሲጠይቁ ነው የዋሉት፡፡ ፈረንጆች፡፡

እነርሱ ምን ያድርጉ በኢትዮጵያ ፓስፖርት ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን የማይፈቀደው ላፕቶፕ እንኳን በውጭ ሀገር ፓስፖርት ለሚገቡ «ኢትዮጵያውያን» ሲፈቀድ ያያሉ፡፡ አበሻ ከመሆን ይልቅ ፈረንጅ መሆን ሲያስከብር አይተዋል፡፡ ታድያ ቢፈረንጁ ምን ይገርማል

Source:Daniel Kibret

Advertisements

About Legesse Habtegiorgis

I wish to see democratic ethiopia.
This entry was posted in Articles. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s