እሌኒ መሐመድ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ደራሲ

በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የሐድያ ገራድ የነበረው ማሒኮ ለንጉሡ ግብር ላለመገበር አሻፈረኝ አለ፡፡ ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዓመታዊውን ግብር እንዲያመጣ ሲጠራው «ወደ ደጅህ አልደርስም፤ ሀገሬንም አልለቅም» ብሎ የንጉሡን መልክተኞች መለሳቸው፡፡ ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የጉዳይቶ ገራድ ወደ ንጉሡ በፍጥነት ገሥግሦ በመሄድ የሐድያ ገራድ ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ደብረ ብርሃን ላይ አረዳው፡፡ ከአካባቢው የባሌና የደዋሮ ገዥዎችም ርዳታ ያገኝ ዘንድ ጠየቀው፡፡
ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ይህንን ሲሰማ የሐድያው ገራድ ዋና ዋና ተባባሪዎች እነማን እንደሆኑ፤ ዐመፁ ሕዝቡን ሁሉ ያስተባበረ ነው ወይስ የጥቂቶች ነው? አንተስ ምን ቢደረግ ይሻላል ትላለህ? ሲል ጠየቀው፡፡ የጉዳይቶው ገራድም ከማሒኮ ጋር የተባበሩ ዘጠኝ ገራዶች መኖራቸውን፤ ማሒኮ ወርዶ አጎቱ ገራድ ባሞ ቢተካ የተሻለ እንደሆነ ነገረው፡፡

ዘርዐ ያዕቆብ ምክሩን ተቀብሎ ባሞን ጠራውና ዋና ገራድ አደረገው፡፡ እርሱንና የጎዳይቶውን ገራድም ሸለማቸው፡፡ ሁለቱንም ሰዎች ከዳሞት ከተንቀሳቀሰ ከብዙ ወታደር ጋር ወደ ሀገራቸው ላካቸው፡፡ የደዋሮና የባሌ ሰዎችም ዐመፀኛው እንዳያመልጥ እንዲከብቡ ተነገራቸው፡፡ ጦሩ ወደ አካባቢው ሲደርስ የገራድ ማሒኮ ተባባሪዎች ድጋፋቸውን ለዘርዐ ያዕቆብ ሰጡ፡፡ ገራድ ማሒኮም ብቻውን ቀረ፡፡
ሁኔታውን የተረዳው ገራድ ማሒኮ በምሥራቅ በኩል ወደ አዳል ሸሸ፡፡ ነገር ግን የዳሞት ሰዎች ተከትለው ድል አደረጉትና ሞተ፡፡ ከዚህ በኋላ የሐድያ ገራዶች ለማዕከላዊው መንግሥት ታማኝ ሆነው ዘለቁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉት አንዱ ገራድ መሐመድ ነበረ፡፡
ገራድ መሐመድ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብና በልጁ በበእደ ማርያም ዘመን የሐድያ ገራድ የነበረ ነው፡፡
ንጉሥ በእደ ማርያም ሥልጣን እንደያዘ ከሐድያ ጋር የነበረውን የክርስቲያኑ መንግሥት ግንኙነት በአንድ እርከን ከፍ አደረገው፡፡ የገራድ መሐመድን ልጅና የገራድ ማሒኮን እኅት «እቴ ዛን ዜላን´ እጅግ በታወቀችበት ስሟም እሌኒን አገባ፡፡ (R. Pankhurst, The Ethiopian Borderlands, 1997, pp.144-146 )
እሌኒ በኢትዮጵያ ታሪክ በአስተዳደር፣ በእምነትና በፖለቲካ ኃያላን ከሆኑ ጥቂት መሪዎች የምትመደብ ናት፡፡ ምናልባትም ከንግሥተ ሳባና ከሕንደኬ ቀጥላ ልትጠቀስ የምትችል ኃያል ሴት ትመስለኛለች፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት እንዲጠናከር፣ በሙስሊሙና ክርስቲያኑ መካከል የነበረው ግንኙነትም የተሻለ እንዲሆን ጥረት አድረጋለች፡፡ ምንም እንኳን የአብራኳ ክፋይ ልጅ ባይኖራት በነገሥታቱና በሕዝቡ ዘንድ እንደ እናት ትታይ ነበር፡፡
ባሏ በእደ ማርያም እሌኒን ከመውደዱ የተነሣ እንደ እናቱ ይሳሳላት እንደነበረ ዜና መዋዕሉ ይነግረናል፡፡ በበእደ ማርያም፣ በናዖድና በልብነ ድንግል ቤተ መንግሥት የእሌኒን ያህል የሚፈራና የሚከበር አልነበረም፡፡ በመፈራቷና በመከበሯም የተነሣ የመንግሥቱ ሽግግር እጅግ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ሰላማዊ እንዲሆን አስችላዋለች፡፡ ዐፄ ናዖድ አርፎ ሕፃኑ ልብነ ድንግል በ12 ዓመቱ ሲነገሥ (1501ዓም) ቤተ መንግሥቱን ትመራው የነበረችው እሌኒ ነበረች፡፡ ዜና መዋዕሉ «የመንግሥቱን ሕግ በደንብ ጠንቅቃ የምታውቅ፣ በሦስት ታላላቅ ነገሥታት ቤተ መንግሥትም የነበረች» ይላታል፡፡ (ሕገ ወሥርዓተ መንግሥት፣ Bodeleian, MS Bruce 88, fol 39r)
በ15ኛው መክዘ አጋማሽ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ፖርቹጋላዊው አልቫሬዝ ይህቺን የሐድያ ልጅ «ብርቱና ታዋቂ ገዥ ነበረች» ይላታል (The Prester John of The Indies, Vol. I, p. 307) ፡፡ እንዲያውም በወቅቱ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ማርቆስ ሕፃኑን ልብነ ድንግልን ወደ ዙፋን ያወጡት እርሳቸውና ንግሥት እሌኒ መሆናቸውን ገልጠውለት ነበር፡፡ «ምክንያቱም ሁሉም ታላላቅ ሰዎችና ሀብት  በእኛ አጅ ነበሩና» ነው ያሉት፡፡ (The Prester John of The Indies. Vol. II, p. 243) የቱርኮችንና የግራኝን ጦር ሁኔታ በማየት ወደ ፖርቱጋል ማቲዎስ የተባለውን መልክተኛ የላከችውም እርሷ ነበረች፡፡ (The Prester John of The Indies, vol. I, p. 39)
ንግሥት እሌኒ ከፖለቲካውና አስተዳደሩ በተጨማሪ በሃይማኖት በኩል ብርቱ ምእመን ነበረች፡፡ አልቫሬዝ እንደሚለው እሌኒ ዓመቱን ሙሉ የምትጾም ሰው ነበረች፡፡ ምግብ የምትመገበውም በሳምንት ሦስት ቀን ማክሰኞ፣ ኀሙስና ቅዳሜ ብቻ ነበር፡፡ (The Prester John of The Indies, vol. II, p. 395) 
ከሁሉም የሚገርመውና ምናልባትም እስከዛሬ በማንም የቤተ መንግሥት ሴት ያልተሞከረው የእሌኒ ችሎታ የነገረ መለኮት ዕውቀቷ ነው፡፡ አልቫሬዝ እንደሚለው እሌኒ በነገረ መለኮት የበሰለችና ከዚያም አልፋ ሁለት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን የጻፈች ሴት ናት፡፡ የመጀመርያው ስለ ምሥጢረ ሥላሴና ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና የተጻፈ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስለ ሕገ እግዚአብሔር የጻፈችው ነው፡፡
እጀግ ብዙው ርስቷ በነበረበት በጎጃም በኋላ ላይ ግራኝ አሕመድ ያፈረሰውን ታላቁን የመርጡለ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አሠርታ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ መንበር ከእንጨት ተሠርቶ በወርቅ የተለበጠ ሲሆን፣ ጽላቱ ከንጹሕ ወርቅ የቀረፀ ነበር፡፡ ይህንን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራትም ባለሞያዎቹን ከግብጽ አስመጥታ ነበር፡፡
የፖርቱጋል መልክተኞች ወደ ኢትዮጵያ በገቡ ጊዜ እሌኒ ስታርፍ በሕዝቡ ዘንድ ድንጋጤ ፈጥሮ ማየቱን አልቫሬዝ ይተርካል፡፡ በደግነቷ፣ በኃያልነቷ፣ በእምነቷና በፖለቲካዊ ጥበቧ የታወቀችው እሌኒ ያረፈችው በመጋቢት 1515 ዓም አካባቢ ነው፡፡ (The Prester John of The Indies, Vol. II, p. 425) እርሷ ማረፏ ሲሰማ ከመላዋ ኢትዮጵያ በመርጡለ ማርያም በሚገኘው መቃብሯ ላይ ለማልቀስ በየቀኑ ሕዝቡ ይጎርፍ ነበር፡፡ ሕዝቡም «እርሷ ስትኖር ሁላችንም እንኖር ነበር፤ እንጠበቅና እንታፈርም ነበር፡፡ እርሷ ከሞተች ግን ሁላችንም ሞትን ማለት ነው፡፡ እርሷ የታላቁም የታናሹም እናትና አባት ነበረችና» እያሉ ሲያለቅሱ ማየቱን አልቫሬዝ ይጽፋል፡፡ (The Prester John of The Indies, vol. II, p. 434) እንዲያውም ካረፈች ከስምንትና ዘጠኝ ወራት በኋላ እንኳን ሰዎች ከተለያየ ቦታ እየመጡ በመቃብሯ ያለቅሱ ነበር፡፡ (The Prester John of The Indies, vol. II,p. 425) 
ቨርጂንያ፣ አሌክሳንድርያ
Advertisements

About Legesse Habtegiorgis

I wish to see democratic ethiopia.
This entry was posted in Articles. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s