ሰው በቁሙ ሐውልት ለምን ያሠራል?

የሕዝቦቻቸውን ድምፅ የማይሰሙ እና ራሳቸው ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ መሪዎች ባሉባቸው ሀገሮች አንድ የተለመደ ክፉ ተግባር አለ፡፡ መሪዎቹ በቁማቸው ሐውልቶቻቸውን ያሠራሉ፡፡ መንገዱን፣ ሕንፃውን፣ ስታዲዮሙን፣ ት\ቤቱን፣ ሆስፒታሉን ሁሉ በስማቸው ይሰይሙታል፡፡ በየሄዱበት ስለ እነርሱ ብቻ ይነገራል፣ ይዘመራል፣ ይጻፋል፡፡ ሀገሪቱ የአንድ ሰው ንብረት እስክትመስል ድረስ፡፡

ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች በቁማቸው እያሉ በሚሊዮን ዶላሮችን አውጥተው ሐውልቶቻቸውን መሥራት ለምን ፈለጉ? ሁሉን የፈጠረ እግዚአብሔር እንኳን ያላደረገውን፣ በግል ገንዘባቸው የሠሩት ይመስል ሁሉን ነገር ለምን በስማቸው ይጠሩታል? ሕዝባቸው ገንዘብ ስለተረፈው ነው? ወይስ ሕዝባቸው በጣም ስለሚወድዳቸው በናንተ ስም ካልሆነ ታንቀን እንሞታለን ስላላቸው ነው?

የእነዚህ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው ከውጭ ሳይሆን ከውስጣቸው የሚመነጭ ነው፡፡ ምንም እንኳን በዙርያቸው የሚገኙ «ራት አግባዎቻቸው» (የአቡነ ጎርጎርዮስ ቋንቋ ነው) ሲያወድሷቸው ቢውሉ እነርሱ ግን በዘመናቸው በጎ እንዳልሠሩ ያውቁታል፡፡ እነዚህ በዙር ያቸው ሆነው እናንተ ካሌላችሁ ዓለም የለችም እያሉ የሚነግሯቸው «ካህናተ ደብተራ» (ቤተ መንግሥትን ተጠግተው ነገሥታቱ ሕግ እንዲጥሱ፣ቅዱሳኑ ከነገሥታቱ እንዲጣሉ ያደርጉ የነበሩ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ካህናት) እንደሚሉት ሳይሆን ሕዝቡ «ንቀልልን» እያለ እንደሚጸልይ ይረዱታል፡፡

እነዚህ አምባ ገነኖች ከሞቱ በኋላ እንኳንስ ሥራቸው ዝክረ ሥራቸው ሁሉ እንደሚረሳ፣ እንደሚመዘበር እና ግብዐተ መሬቱ አብሯቸው እንደሚፈጸም ነፍሳቸው ትነግራ ቸዋለች፡፡ ነፍስን ማታለል አይቻልምና፡፡ ከነፍስ ጠባያት አንዱ ዐዋቂነት ነው፡፡ ዐዋቂት ነፍስን ከውጭም ከውስጥም የሚመጣ ከንቱ ውዳሴ፣ የሐሰት ሪፖርት፣ የማስመሰያ ተኩስ እና የማታለያ ስሜት አያታልላትም፡፡ እርሷ ምንጊዜም ትክክለኛውን ነገር ብቻ ትረዳለች፡፡

እነዚህ ሰዎች ወደ ቤታቸው ሲገቡ፤ አልጋቸው ላይ ሲወጡ፣ መጸዳጃ ቤት ሲቀመጡ፣ ወይንም በሌላ መንገድ ለብቻቸው የሚሆኑበት አጋጣሚ ሲፈጠር ነፍሳቸው እውነታውን ታረዳቸዋለች፡፡

እናም ከሞቱ በኋላ ለእነርሱ ሐውልት የሚያቆም፣ መንገድ በስማቸው የሚሰይም፣ በየዓመቱ በዓላቸውን የሚያከብር፣ ዝክረ ታሪካቸውን የሚያስታውስ ትውልድ እንደ ማይኖር ይገባቸዋል፡፡ ጅብ ለምን ሌሊት ይሄዳል ቢሉ ቀን የሚሠራውን ስለሚያውቅ ነው እንደሚባለው፡፡

እነዚህ ሰዎች ዘመናቸው ከሞቱ በኋላ እንደማትቀጥል ያውቋታል፡፡ ኃይላቸው ሲደክም ጀንበራቸው እንደምትጠልቅ ተረድተውታል፡፡ እናም ሲሞቱ ሐውልት እንደ ማይቆ ምላቸው ስሚያውቁት በቁማቸው ሐውልታቸውን ማቆም ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሐውልታቸው ከሞቱ በኋላ እንደማይኖር ቢያውቁት እንኳን በቁም ተዝካራቸውን ማውጣት ይመርጣሉ፡፡

ከሞቱ በኋላ ሥራቸው እንደሚቀጥል ያወቁ ቅዱሳን፣ ሰማዕታት፣ ጻድቃን፣ መሪዎች፣ ደራስያን፣ ሰዓልያን፣ አርበኞች ለፈጣሪያቸው፣ ለሕዝባቸው እና ለሀገራቸው ስለሚያከ ናውኑት በጎ ሥራ እንጂ ስለሚዘከረው ስማቸው አይጨነቁም፡፡ ከበጎ ሥራ በላይረዥ ዘመን የሚኖር ሐውልት እንደሌለ ያውቃሉ፡፡ ስለሚዘከረው ስማቸው ሳይሆን ስለሚጠቀመው ሕዝባቸው ይጨነቃሉ፡፡ ስለ እነርሱ ስም ሳይሆን ስለ ሃይማኖታቸው፣ ሀገራቸው፣ ሕዝባቸው የክብር ስም ይጨነቃሉ፡፡

በጣም በሚገርም ሁኔታ ሐውልታቸውን ራሳቸው ካቆሙ ሰዎች ይልቅ ሐውልታቸውን ተተኪው ትውልድ ያቆመላቸው ሰዎች እስከ ዛሬ ይታወሳሉ፣ ይከበራሉ፡፡ ዐፄ ምኒሊክ ባቡር ሲያስገቡ፣ ስልክ ሲያስመጡ፣ መንገድ ሲያሠሩ፣ ት/ቤት ሲያስገነቡ፣ ሆስፒታል ሲያቆሙ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲያስተክሉ ኖሩ፡፡ ለዚህ በጎ ሥራቸው ከሞቱ በኋላ ትውልዱ «እምዬ ምኒሊክ» እያለ የማይጠፋ ስም ሰጣቸው፡፡ ሐውልታቸውን አቆመላቸው፡፡ በ1984 ዓም አካባቢ የመንግሥትን ለውጥ ተጠቅመው ጥቂት እበላ ባዮች ሐውልታቸውን እናወርዳለን ብለው ሲነሡ ሕዝብ እንደ አራስ ነበር ተቆጥቶ፣ እንደ ንብ መንጋ ተቆጭቶ ነበር የተነሣባቸው፡፡

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን አበው የእግዚአብሔር ስም እንዲከብር፣ የቀደሙት አባቶቻቸው ስም እንዲዘከር እንጂ ስለራሳቸው ስም ተጨንቀው አያውቁም ነበር፡፡ አብርሃ እና አጽብሐ በራሳቸው ስም ቤተ ክርስቲያን አልሠሩም፡፡ የኋላ ሰዎች ግን መልካሙን ሥራቸውን አይተው በስማቸው ታቦት ቀረጹላቸው፡፡

ሐውልት በቁም መሥራት የክብር መለኪያ፣ የሥራ ማሳያ ቢሆን ኖሮ ከአንድ ወጥ ዐለት አሥራ አንድ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ያነፀው ቅዱስ ላሊበላ ቢያንስ አንድ ሐውልት ለራሱ ባቆመ ነበር፡፡ እርሱ የፈጣሪው ስም የሚሠራበትን ሠራ፡፡ ፈጣሪውም የላሊበላ ስም የሚጠራበትን መታሰቢያ አደረገለት፡፡ ይኼው በዕለተ ገና ስሙ ለዘለዓለም ሲዘከር ይኖራል፡፡ የራሳቸውን ሐውልት ለመሥራት የሚጨነቁት እንደ ላሊበላ ለፈጣሪያቸው የሚያቀርቡት አምኃ የሌላቸው ናቸው፡፡

ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ደብረ አስቦ ዋሻ ገብተው ሲጋደሉ በስማቸው ገዳም አልገደሙም፡፡ ያነፁት በእመቤታችን ስም የሚጠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በስማቸው ታቦት የተቀረጸው፣ ቤተ ክርስቲያን የታነፀው ካረፉ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው፡፡ እርሳቸው 500 ዓመታት ሊዘልቅ የሚችል የቁም ሐውልት ስለ መሥራት አልተጨነቁም፡፡ ከጽድቅ በላይ ምን ሐውልት አለና፡፡ ዛሬ ግን ስማቸው ከ500 ዓመታት በላይ ተሻግሮ በመላው ዓለም ይጠራል፡፡

ከጎንደር ነገሥታት ሁሉ አያሌ አብያተ ክርስቲያናትን በማሠራት፣ ገዳማትን በመገደም፣ ለብዙዎቹ ነገሥታት አንጋሽ እና ጠባቂ በመሆን እቴጌ ምንትዋብን የሚስተካከላት የለም፡፡ ናርጋ ሥላሴ፣ ክብራን ገብርኤል እና የጎንደርዋ ቁስቋም ደብር እስከ ዛሬም ታሪክዋን በህያውነት ይመሰክሩላታል፡፡ በዲፕሎማሲው፣ በኪነ ሕንፃው፣ በሥነ ጽሑፉ፣ በሥነ ሥዕሉ እና በትርጓሜ መጻሕፍቱ ሁሉ ከእርሷ በኋላ ማንም ያልተካውን ሥራ ሠርታለች፡፡

ለዚህ ሁሉ ሥራዋ ግን ሐውልት አላቆመችም፤ ስለ እርሷ የምናገኘው ሥዕል እንኳን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ሥር በተማኅጽኖ ሰግዳ፣ እመቤታችንን ከፍ፣ ራስዋን ዝቅ ያደረገችበትን የትኅትና ሥዕሏን ነው፡፡ እርስዋ በትኅትና ዝቅ ብትልም፣ በጎ ሥራዋ ግን ከሦስት መቶ ዓመታትም በኋላ ከትውልዶች በላይ ከፍ ብሎ ማነነቷን ይመሰክራል፡፡

የራሽያ ኮሚኒስት መሪዎች ስማቸውን ከዘመናት በላይ ለማስጠራት ሲሉ ከተማውን ሁሉ በስማቸው ጠርተውት ነበር፡፡ በየመንገዱ ሐውልታቸው ቆሞ ነበር፡፡ ፎቶዎቻቸው ዓይን እስኪያሰለቹ ድረስ በመላ ሀገሪቱ ተሰቅለው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከሰባ ዓመታት በላይ መዝለቅ አልቻሉም፡፡ ዛሬ በስማቸው የጠሯቸው ከተሞች ተቀይረዋል፤ ሐውልቶቻቸው ፈርሰዋል፣ ፎቶዎቻቸው የዕቃ መጠቅለያ ሆነዋል፡፡ ዝክረ ስማቸውም ተረስቷል፡፡ የሚያስታውሰውም ካለ በበጎ አያነሣውም፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገርሙኝ ነገሮች አንዱ የተፈሪ መኮንን ት/ቤት ጉዳይ ነው፡፡ ያንን ት/ቤት ደርግ መጣና «እንጦጦ አጠቃላይ» ብሎ ሰየመው፡፡ እስካሁን ግን የትኛ ውንም ባለታክሲ «እንጦጦ አጠቃላይ ውሰደኝ» ብትሉት እንጦጦ ተራራ ይወስዳችሁ ይሆናል እንጂ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት አይወስዳችሁም፡፡ መንግሥት ቢቀይረው እንኳን ሕዝቡ አልተቀበለውም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው «ስድስት ኪሎ፣ ተፈሪ መኮንን» እያለ ታክሲው የሚጠራው፡፡

ይህ ነገር አንድ ቁም ነገር እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ ሐውልትን እድሜ የሚሰጠው ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መልስ፡፡ አንድን መታሰቢያ ረዥም ዘመን እንዲኖር የሚያደርገው የተሠራበት ቁሳቁስ አይደለም፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት እንጂ፡፡ እንደ ሳዳም ሐውልት በውድ ዋጋ የተሠራ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ዛሬ የለም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መንግሥት ያልሰየማቸው ሕዝቡ ግን ለመታሰቢያነት የሚጠራቸው ስንት አካባቢዎች፣ መንገዶች፣ አደባባዮች አሉ፡፡ መንግሥት ያለ ሕዝቡ ተቀባይነት ሐውልት ያቆመለት ማርክስ ግን ሐውልቱን ከነመኖሩ የሚያስታውሰው የለም፡፡ ጥቁር አንበሳ አጠገብ ያለው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሐውልትም ተረስቷል፡፡

 

Advertisements

About Legesse Habtegiorgis

I wish to see democratic ethiopia.
This entry was posted in Articles. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s